አምባሳደር ዶ/ር ገነት ተሾመ በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ ጋር ተወያዩ፣

(ጥቅምት 4 ቀን 2015 ዓ.ም) በኩባ የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክቡር ዶ/ር ገነት ተሾመ በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ ጋር ሀገራችን ከኩባ ጋር በግብርና ዘርፍ በትብብር መስራት የምትችልባቸውን ጉዳዮች ለመለየት የሚያስችል ውይይት አካሄዱ።

በውይይቱ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ሀገራችን በግብርናው ዘርፍ ለመተግበር ባወጣችው የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ እየተመራች በስንዴ እና አረንጓዴ አሻራ ዘርፍ ውጤታማ ስራዎች ማከናወኗን በማውሳት፣ በእንስሳት ሃብት ልማትና ጤና ማሻሻል ዘርፍ የተቀመጡ ዕቅዶችን ከግብ ለማድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ መስራት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም አምባሳደር ዶ/ር ገነት ወደ ጽ/ቤታቸው በማቅናት በግብርናው ዘርፍ ሀገራችን የምትፈልጋቸውን ድጋፎች ለመለየት የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸውንም አድንቀዋል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያና ኩባ መካከል በግብርና ዘርፍ የነበሩ የትብበር መስኮችን አስመልክቶ በግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ በሆኑት ዶ/ር ዓለማየሁ መኮንን አማካኝነት ዝርዝር ገለጻ ተደርጓል። በዚሁ መሰረት ኩባ ቀደም ሲል በተለይም በደርግ ዘመነ መንግስት በግብርናው ዘርፍ የነበረውን የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት ለመቅረፍ የሀገራችንን ባለሙያዎች በማሰልጠንና የማሰልጠኛ ተቋማትን በመገንባት ያደረገችው አስተዋጽኦ አድናቆት ተችሮታል። ከሰው ሀይል ልማት በተጨማሪም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማስፋፋት፣ እንዲሁም በምርጥ ዘር አቅርቦት ዙሪያ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸው ተወስቷል።

ገለጻውን ተከትሎ በተደረገ ሰፊ ውይይት በቀጣይነት በሀገራቱ መካከል በግብርና ግብአት አቅርቦት፣ ዝርያ ማሻሻል፣ ባዮ ቴክኖሎጂና መኖ ልማት ወዘተ መስኮች ዙሪያ ተቀራርቦ መስራት የሚቻልበት ዕድል መኖሩ ተመላክቷል።

አምባሳደር ዶ/ር ገነት በበኩላቸው ኩባዎች ለሀገራችን ዳር ድንበር መከበርም ሆነ ለሀገራችን የልማት እንቅስቃሴ ያበረከቱትን ታሪካዊ አስተዋጽኦ በመጥቀስ፣ በአሁኑ ወቅትም ሀገራችንን በተለያዩ ዘርፎች የመደገፍ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም ሁለቱ ሀገራት በግብርናው ዘርፍ ትብብር ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት የተፈራረሙ መሆናቸውን በማውሳት፣ በአሁኑ ወቅትም በተመረጡ 10 መስኮች ትብበር ማድረግ የሚያስችል ረቂቅ የመግባቢያ ስምምነት ከኩባ ወገን ለኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር መላኩን አሳውቀዋል። በቀጣይነትም በግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ ሃላፊዎች የተደረገላቸውን ገለጻ፣ እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ ሀገራችን ያስቀመጠችውን የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ መነሻ በማድረግ በዘርፉ የሀገራችንን ጥቅም ለማስከበር ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram